የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው ጉባኤ በሰው ልጅ አመጣጥ ሳይንስ ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ፣ በምርምርና በትምህርት ዘርፍ ለአለም ያበረከቱትን የዕድሜ ልክ አገልግሎት እንዲሁም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ምድር መሆኗን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስታወቅ ላደረጉት ታላቅ ሚና ዕውቅና በመስጠት ለፕሮፌሰር ዶናልድ ካርል ጆሃንሰን የክብር የሳይንስ ዶክትሬት (Doctor of Science, Honoris Causa) ዲግሪ ሰጥቷል።
ፕሮፌሰር ጆሃንሰን በ1974 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አፋር ክልል ውስጥ “ሉሲ” ወይም “ድንቅነሽ” በመባል የምትታወቀውን የ3.2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላት የሰው ዘር ቅሪተ አካል በማግኘታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ሆነዋል። ይህ ግኝት የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥን የሚመለከቱ ሳይንሳዊ እውቀቶችን በእጅጉ የቀየረ ሲሆን፣ የቀደሙ የሰው ዝርያዎች አእምሯቸው ከማደጉ በፊት በሁለት እግራቸው ቀጥ ብለው ይራመዱ እንደነበር ለማረጋገጥ ወሳኝ ማስረጃ ሆኗል።
ፕሮፌሰር ጆሃንሰን ከቺካጎ ዩኒቨርሲቲ በአንትሮፖሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል። በኋላም በሰው ልጅ መገኛ ጥናት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ያለውን የሉሲን ግኝት በማሳካት ለሳይንሱ ዘርፍ የማይረሳ አሻራ አስቀምጠዋል። ፕሮፌሰር ጆሃንሰን በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዝግመተ ለውጥና ማኅበራዊ ለውጥ ትምህርት ቤት (School of Human Evolution and Social Change) የክብር ፕሮፌሰር (Professor Emeritus) ሲሆኑ፣ እንዲሁም የ የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት ተቋም (Institute of Human Origins) መስራች ዳይሬክተር ናቸው።
“Lucy: The Beginnings of Humankind” የተሰኘውን መጽሀፍ ጨምሮ በርካታ ሳይንሳዊ ሥራዎችን በማበርከት፣ በማስተማርና ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑ የሳይንስ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ሳይንስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያን ቅርሶች ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ጆሃንሰን ለሰው ልጅ መገኛ ሳይንስ ያበረከቱትን ታላቅ አስተዋፅኦ፣ በሰው ዘር መነሻ ጥናት ውስጥ የኢትዮጵያን ሚና በማጉላት ያሳዩትን ክብር እና ለዓለም አቀፍ ትምህርትና ምርምር ያበረከቱትን ልዩ አገልግሎት በማድነቅ ይህንን ከፍተኛ ክብር አበርክቶላቸዋል።
Source: FastMereja









No comments yet.