የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎች ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ ተገለፀ!

- Advertisement -
Sidebar AD

Fastmereja:-በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተዘረጋው የኢትዮጵያ የሠራተኛ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት (ELMIS) አፈጻጸም ችግር እና በአመራሩ ላይ በሚታይ ችግር ምክንያት፣ የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዘርፍና የአገናኝ ኤጀንሲዎች ህልውና በአስጊ ሁኔታ ላይ መውደቁን የሕብረት ኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ኤጀንቶች አሰሪ ማህበር አስታወቀ።

ማህበሩ ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጁፒተር ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ ኤጀንሲዎች በአዲሱ አዋጅ መሠረት ተገቢውን የዋስትና ገንዘብ አስገብተው ወደ ሥራ ቢገቡም፣ በአሁኑ ወቅት ህልውናቸውን የሚፈታተኑ ጽኑ አሠራራዊ እንቅፋቶች እየገጠሟቸው መሆኑን ገልጿል።

ማህበሩ መግለጫው ላይ ያነሳቸው ዋና ዋና መዋቅራዊና አሠራራዊ ችግሮች ኤጀንሲዎች በ4 ባንኮች ብቻ መወሰናቸው፣ አገልግሎት ላኪ ሆነው ሳለ VAT መጣሉና የኮሚሽን ተመን በሚኒስቴሩ መወሰኑ ዘርፉን እንደፈተነው ያስታወቀ ሲሆን በተጨማሪም በውጭ ምንዛሪ መዘግየትና በELMIS ሲስተም ሳቢያ ከ90 በመቶ በላይ ኤጀንሲዎች ከሥራ መታገዳቸውን ገልጿል።

እንዲሁም ከ1,000 ዶላር በታች ጎድሏል በሚል ፈቃድ መታገዱ የሥራ ዕድልን እያጨናገፈ መሆኑን የጠቆመው ማህበሩ፤ ባለድርሻ አካላት ከመመሪያ ዝግጅት መገለላቸው ሕገወጥ የሰዎች ስምሪትን ያፋጥናል ሲል አስጠንቅቋል።

ማህበሩ በማጠቃለያው፣ መንግስት ወጣቶች በሥራ ላይ እንዲሰማሩና ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ የጀመረውን ቁርጠኝነት እንደሚደግፍ ገልጾ፤ ሆኖም ባለፉት አራት ወራት የታየው ችግርና ዘርፉን ለሌላ ዓላማ ለማዋል በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች የሚታየው የበላይነት የተጀመረውን ጉዞ የሚያደናቅፍ በመሆኑ የመንግስት አስቸኳይ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ብሏል።

በመሆኑም በቴክኖሎጂ ወይም በAI የተደገፉ ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ፣ በአዋጅና በመመሪያው አተገባበር ላይ የተነሱትን ችግሮች ለመፍታት የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ቁርጠኛ ውሳኔና አፋጣኝ ጣልቃ ገብነት እንዲያደርጉ ማህበሩ በአጽንኦት ጥሪ አቅርቧል።






Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2