#Ethiopia | ኢትዮጵያ ያላትን የኤቪዬሽን፣ የከተማ መሠረተ-ልማት እና የኢንቨስትመንት ዕድሎች በመጠቀም በሜዲካል ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ እምቅ አቅም እንዳላት ቢጠቆምም፤ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግና ሀገሪቱን ቀጣዩ የሕክምና ማዕከል ለማድረግ የመንግስት የፖሊሲ ድጋፍ እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት እገዛ እጅግ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ያለውን የህክምና ዘርፍ ክፍተት ለመሙላት እና የውጭ ሀገር ህክምናዎችን በተቀላጠፈ መልኩ ለማመቻቸት ላለፉት 12 ዓመታት ሲሰራ የቆየው ጌትዌይ ሜዲካል ትራቭል፣ በሀገሪቱ የሜዲካል ቱሪዝምን ለማስፋፋት አዳዲስ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል።
የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ዶክተር በጋሻው ባይለየኝ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በቴክኖሎጂ፣ በባለሙያ ልምድ እንዲሁም በከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማነስ ምክንያት ዜጎች የሚፈልጉትን ሙሉ የህክምና አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ስቃይና ለህይወት ማለፍ እየተዳረጉ ነው።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም ድርጅታቸው እንደ ህንድ፣ ታይላንድ እና ቱርክ ካሉ ሀገራት በተጨማሪ፣ በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አጅማን ከሚገኘው ታዋቂው ቱምቤይ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ጋር አዲስ የትብብር ትስስር ፈጥሯል።
ይህ በተባበሩት አረብ ኢምሬት የሚገኘው ትልቅ የህክምና ተቋም በተለይ በኒውሮ ሳይንስ፣ በአጥንት ህክምና እና በሪሃቢሊቴሽን ዘርፎች ላይ የላቀ ስም ያለው ሲሆን፣ ከጌትዌይ ሜዲካል ትራቭል ጋር በመተባበር ሁለት ታዋቂ ስፔሻሊስት ዶክተሮቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኳል።
እነዚህ የውጭ ሀገር ሃኪሞች በአያት አካባቢ በሚገኘው ኑቢራ የህክምና ማዕከል በመገኘት በህብለሰረሰር እና በአጥንት ህክምና ዙሪያ ለታካሚዎች ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ እዚህ ካሉ የሀገር ውስጥ ኒውሮ ሰርጀኖች እና ኦርቶፔዲክ ሰርጀኖች ጋር የልምድ ልውውጥና የስልጠና መርሃ ግብር እያካሄዱ ይገኛሉ።
ጌትዌይ ሜዲካል ትራቭል ከዚህ ቀደምም ከ50 በላይ ኢትዮጵያውያን ሃኪሞችን ወደ ውጭ ሀገር ልኮ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ማመቻቸቱ ይታወሳል።
ዶክተር በጋሻው እንደሚያምኑት፣ የጤና ሚኒስቴር በሀገሪቱ የሜዲካል ቱሪዝምን ለመገንባት የሚያደርገው ጥረት እጅግ የሚበረታታ ከመሆኑም በላይ እንዲያውም “ዘግይተናል” የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሰለ የኤቪዬሽን መታደሏ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት እንዲሁም በዘርፉ ላይ እየታዩ ያሉ የኢንቨስትመንት ለውጦች ሀገሪቱ በሜዲካል ቱሪዝም እንድታድግ ትልቅ መሰረቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ ዘርፉ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የመንግስት የፖሊሲና የስትራቴጂ ድጋፍ እንዲሁም የባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት እገዛ እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህ ከተሳካ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የውጭ ዜጎች ጭምር መጥተው የሚታከሙባትና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝባት የህክምና ማዕከል መሆን እንደምትችል በልበ ሙሉነት ገልጸዋል።
በጌትነት ተመስገን
📷ከበደ መክብብ
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu #ጌጡ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.