አድናቂም ወዳጅ ይሆናል!

- Advertisement -
Sidebar AD

ጊዜው በ90 ዎቹ መጀመሪያ ግድም ነው፡፡ በቢሾፍቱ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሳለን በሀገራችን ታዋቂ ከሚባሉት የሙዚቃ ባንዶች አንዱ የሜጋ አምፊ ቲያትር ራሚድ ባንድ ነበር።

አንድ ቀን ዝነኛው ራሚድ ባንድ የሙዚቃ ድግሱን ለማቅረብ፣ ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ መጥቶ ነበር፡፡ ከባንዱ ጋር ዝግጅታቸውን ሊያቀርቡ ከመጡት ተወዳጅና ታዋቂ አርቲስቶች መካከል፡- ላፎንቴኖች ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ ፣ ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ፣ መልካሙ ተበጀ ፣ ጀማል መሀመድ(አቺኩዳ)፣ ፀደንያ ገ/ማርቆስ ፣ ማናልቦሽ ዲቦ፣ ደረጀና ሀብቴ፣ጥላሁን እልፍነህ ፣ ዘውዱ በቀለና ፊሊፕ ማርቲን ይገኙበታል፡፡

የሙዚቃ ዝግጅቱን ለመታደም የከተማችን ነዋሪ በወረፋ ነበር ወደ አዳራሹ የገባው፡፡ እኔም ዝግጅቱን በገጉት ሲጠባበቁ ከነበሩት መካከል አንዱ ነኝ፡፡ አርቲስቶችን ለማስፈረም ሁሉ በኪሴ በቂ ወረቀቶችን ይዤ ነበር የገባሁት፡፡ በወቅቱ ሁሉንም አርቲስቶች የማደንቅ ቢሆንም፣ በተለይ ደግሞ ኮሜዲያን ደረጀንና ሃብቴን ለማየትና ከተቻለም ለማስፈረም በእጅጉ ጓጉቼ ነበር።

በመጨረሻም በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ታላቅ የሙዚቃ ድግስ በይፋ ተጀመረ፡፡ እውነት ለመናገር አንድም ቤቱ የቀረ የቢሾፍቱ ነዋሪ ያለ አይመስልም ነበር፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ የምናቃቸው ተወዳጅና ዝነኛ ድምጻውያን በየተራ መድረክ ላይ እየወጡ አቀነቀኑ፡፡ ታዳሚው አብሯቸው እየዘፈነ እንደጉድ ጨፈረ፡፡ አዳራሹን በአንድ እግሩ አቆመው፡፡

የመድረክ አጋፋሪው ጥላሁን እልፍነህ፣ በመቀጠል ሥራቸውን የሚያቀርቡት ሁለቱ ተወዳጅ ኮሜዲያን እንደሆኑ ሲያስተዋውቅ፣ ታዳሚው በጩኸትና በፉጨት ደስታውንና ፍቅሩን ገለጸ፡፡ ደረጀና ሃብቴም ወደ መድረኩ ወጥተው በማያልቀው ቀልዳቸውና ለዛቸው አዳራሹን በሳቅ ሞሉት፡፡

ሥራቸውን አቅርበው እንደጨረሱ ከተጠገጠገው ሰው መሃል እንዴት ተፈትልኬ እንደወጣሁ ሳላውቀው፣ ራሴን መድረኩ አጠገብ አገኘሁት፡፡ ከዚያም አሻቅቤ ወደ ደረጀና ሃብቴ እየተመለከትኩ፣ “ፈርሙልኝ” አልኳቸው – ያዘጋጀሁትን ወረቀት ዘርግቼ፡፡ አንዳቸው ስሜን ጠየቁኝ፡፡ ነገርኳቸው፡፡ ከዚያም ከመድረኩ ጀርባ (ባክ ስቴጅ)ይዘውኝ ገቡ። እዚያ ሌሎችም ታዋቂ አርቲስቶች ነበሩ፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅሜ ሁሉንም አስፈረምኳቸው፡፡

ተልዕኮዬን አጠናቅቄ ከመሄዴ በፊት ግን ኮሜዲያን ሀብቴ ምትኩ ለእነርሱ ከተዘጋጀው ሳንዱች ላይ አንስቶ እንድበላ ጋበዘኝ፡፡ በጣም ነበር ደስ ያለኝ፡፡ በአንዳች በማላውቀው ስሜት ተጥለቅልቄ ነበር፡፡ በቲቪ ብቻ እያየኋቸው የማደንቃቸውና የምወዳቸው ደረጀና ሀብቴ፣ የቅርብ ጓደኞቼ የሆኑ ያህል ተሰምቶኝ ነበር ብል ፈጽሞ አላጋነንኩም፡፡

ከዚያን ጊዜ በኋላ ታዲያ ደረጀና ሃብቴ እንዲሁም ሌሎች አርቲስቶች የፈረሙልኝን ወረቀት ት/ቤት ድረስ በመውሰድ ለጓደኞቼ እያሳየሁ፣ “ደረጃዬን” እንዲያውቁልኝ እጋጋጥ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ “እኔኮ ከደረጄና ሃብቴ ጋር ጓደኛ ነኝ” እያልኩኝ፣ አብሬያቸው ሳንድዊች መብላቴን ሁሉ በማስረጃነት አቀርብ ነበር፡፡

ይሄ ሁሉ የሆነው በታዳጊነት ዕድሜ ላይ ነው – በተማሪነት ዘመን፡፡ ዛሬ ላይ ተወዳጁ ኮሜዲያን ደረጀ የቅርብ ጓደኛዬና ወዳጄ ብቻ ሳይሆን ወንድሜም ጭምር ነው፡፡

ደሬ፤ እንኳን ተወለድክልን !

ረዥም ዕድሜና ጤና እመኝልሃለሁ!

አክባሪህና ወዳጅህ ቴዎድሮስ ታደሰ አየለ





Source: FastMereja

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom1