#Ethiopia | አሜሪካ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት በማጠናከር በአህጉሪቱ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የጸጥታና የደኅንነት ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ጋር በመተባበር ያዘጋጀችው የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። ሲምፖዚየሙ ከሐምሌ 20 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የሲምፖዚየሙ ዋና ትኩረት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን አቅምን ማሳደግ፣ እንዲሁም የአፍሪካ የጸጥታ ተግዳሮቶችን በጋራ መመከት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መመካከር ነው።
በሲምፖዚየሙ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን፣ የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናንት ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል እና ሌሎች የጦር መሪዎች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በመክፈቻው ላይ እንደገለጹት፣ የአፍሪካን የጸጥታና የደኅንነት ተግዳሮቶች ለመቋቋም በአህጉሪቱና በዓለም አቀፍ አጋሮች መካከል ጠንካራ ትብብር መገንባት ያስፈልጋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፣ ሲምፖዚየሙ በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ዘላቂ አጋርነትን ለማጠናከር፣ የመከላከያ ተቋማትን ለማሻሻል፣ ወታደራዊ ትምህርትን ለማስፋፋትና ዘላቂ የመከላከያ አቅምን ለማሳደግ ጠቃሚ መድረክ ነው።
አሜሪካ ለአፍሪካ ሀገራት የምታደርገውን የመከላከያ ድጋፍ በማጠናከር የወታደራዊ ዝግጁነትን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗንም አስታውቀዋል።
በተለይም ሽብርተኝነት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የሳይበር ጥቃትና የተለያዩ ግጭቶችን ለመመከት የጋራ ትብብርና የተጠናከረ የጸጥታ አቅም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም በመንግሥታት፣ በወታደራዊ ተቋማት፣ በግሉ ዘርፍና በተለያዩ አጋር አካላት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተገልጿል።
Source: GetuTemesgen









No comments yet.