የ 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተናን በወረቀት ለመውሰድ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ ተፈታኝ ተማሪዎች በፌዴራል እና በክልሉ ፖሊስ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን በመግለፅ የፀጥታ ስጋት እንደሌለባቸው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ለአሐዱ አስታውቋል።
በትምህርት ሚኒስቴር እና በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ለሶስት ሳምንታት ያክል በስድስት ዙር ሲሰጥ የቆየው የኦንላይን በይነ መረብ ፈተና ባለፈው ሳምንት መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለተኛውን ዙር በወረቀት የሚሰጠውን ፈተና ለመፈተን ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው እየገቡ መሆኑን የገለፁት የዩኒቨርስቲው ኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መምህር ያፌት ታደሰ ናቸው።
በዮኒቨርሲቲው ሁለቱም ካምፓሶች ብዛት ያላቸው የፌዴራል እና የክልሉ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ሌሎች የበጎ ስራ የሚሰሩ መኖራቸውንተናግረዋል።
ከፀጥታ አካላት በተጨማሪ ፈተናውን የሚያስተባብሩ አካላት በቅርበት እየተከታተሉና ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን የገለፁሲሆን ከዚህ በፊት የነበሩ ፈተናዎችንም ያለ ፀጥታ ችግር የተከናወኑ በመሆናቸው አሁንም በሰላም ተፈትነው እንደሚወጡ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ለመቀበል አስቀድሞ የምግብ አቅርቦትን ማሟላት ጨምሮ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ ከትናንት ጀምሮ አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ መሆኑን ተናግረዋል።
የተማሪዎች አቀባበል እስከ ዛሬ ማለትም ሐምሌ 21 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ሲሆን በአጠቃላይበሁሉቱም ካምፖሶች 7ሺህ 700 አካባቢ ተማሪዎችን እንደሚቀበል አስታውቀዋል።
በትግራይ ክልል ለሚገኙ የ12 ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናው በመቀሌ እና አክሱም ዩኒቨርስቲ እንደሚሰጥ በመግለፅ ከአዲግራት ጫፍ ጀምሮ እስከ ራያ አካባቢ ያሉ አብዛኞቹ ተማሪዎች ወደ መቀሌ እንደሚገቡ ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም ከተማሪዎች ቅበላ አስቀድሞ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ለተላኩ የፈተና ክፍል ሀላፊዎችና ከመላው ኢትዮጵያ ለተውጣጡ ፈታኞች አቀባበል መደረጉን አስታውቀዋል።
#አሐዱ
Source: Yeneta Tube









No comments yet.