”በወር ውስጥ በተደጋጋሚ ካርድ ሲገዛ የሚታየው የዋጋ ልዩነት የሲስተሙ የ30 ቀናት አጠቃላይ ፍጆታ ስሌት ውጤት ነው” አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
የቅድመ-ክፍያ (Smart Card) ቆጣሪ ተጠቃሚዎች በአንድ ወር ውስጥ ደጋግመው ኤሌክትሪክ ሲገዙ የሚፈጠረው የዋጋ ወይም የኪሎ ዋት ሰዓት መጠን ልዩነት የወርሃዊ ፍጆታ አሰራር ውጤት መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ይኸይስ ስዩም ከኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ደንበኞች በአንድ ወር ውስጥ በተደጋጋሚ ኃይል ሲገዙ ስለሚገጥማቸው የዋጋ ልዩነት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የዋጋ አተማመን ሥርዓቱ በ30 ቀናት ውስጥ የተጠቀሙትን አጠቃላይ የኃይል መጠን በአንድ ላይ ደምሮ ስለሚያሰላው፣ በአንድ ወር ውስጥ ደጋግመው ካርድ ሲሞሉና የኪሎ ዋት መጠኑ ሲጨምር ታሪፉም አብሮ ይጨምራል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ይኸይስ የኃይል ክፍያው የሚሰላው ደረጃ በደረጃ በሚያድግ የታሪፍ እርከን መሆኑን ገልጸዋል ።
“በዚህም መሠረት ደንበኞች በወሩ መጀመሪያ ላይ ለሚያደርጉት የመጀመሪያ ግዢ ዝቅተኛው የታሪፍ ተመን የሚተገበርላቸው ሲሆን፣ በዚያው ወር ውስጥ ለሁለተኛ ወይም ለሦስተኛ ጊዜ ተጨማሪ ኃይል ሲገዙ ግን ቀደም ሲል የተጠቀሙት የኃይል መጠን ተደምሮ ወደ ከፍተኛው የታሪፍ እርከን ስለሚያሸጋግራቸውና የቫት ክፍያ ውስጥ ስለሚገቡ ለተመሳሳይ የገንዘብ መጠን የሚሰጣቸው የኪሎ ዋት መጠን አነስተኛ ይሆናል” ብለዋል።
እድላዊት ብርሃኑ

Source: Yeneta Tube









No comments yet.