በኬንያ 15 ዝሆኖችን የገደለው ምስጢር ተገለጠ፤ የመጀመሪያ የላቦራቶሪ ውጤት ሳይናይድ መርዝን አመለከተ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | በኬንያ ደቡባዊ ክፍል በሚገኘው አምቦሴሊ የሥነ ምህዳር አካባቢ በባለፈው አንድ ወር ውስጥ 15 ዝሆኖች በተከታታይ ከሞቱ በኋላ ሲደረግ የቆየው ምርመራ የመጀመሪያ ውጤት የሞታቸው ምክንያት ከፍተኛ መርዛማ የሆነው ሳይናይድ (Cyanide) መሆኑን አመልክቷል።

የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን (KWS) እንደገለጸው፣ በዝሆኖቹ አካል ላይ በተደረገ የመጀመሪያ የላቦራቶሪ ምርመራ የሳይናይድ ንጥረ ነገር ተገኝቷል።

ምርመራው እንደሚያመለክተውም ዝሆኖቹ በአካባቢው እርሻዎች ላይ በኬሚካል የተረጩ ቲማቲሞችን ከበሉ በኋላ ሊመረዙ እንደቻሉ ጠንካራ ግምት አለ።

በአንድ የዝሆን ሆድ ውስጥ ብዙ ቲማቲሞች መገኘታቸውም ይህንን ግምት እንደሚደግፍ ተገልጿል።

የKWS ዋና ዳይሬክተር ኤሩስቱስ ካንጋ እንደተናገሩት፣ ሳይናይድ በጣም ፈጣን እና ከባድ ጉዳት የሚያደርስ መርዝ ሲሆን፣ ይህ ክስተት በዝሆኖች ብቻ ሳይወሰን በአካባቢው በሚግጡ የቤት እንስሳትና በሌሎች የዱር እንስሳት ላይም አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ባለስልጣናቱ ግን መርዙ ሆን ተብሎ በአርሶ አደሮች ተቀምጦ ወይም በአጋጣሚ የተከሰተ መሆኑን ገና እንዳላረጋገጡ ገልጸዋል።

የኬሚካሉ ምንጭ፣ ወደ ቲማቲሞቹ የደረሰበት መንገድ እና ኃላፊው ማን እንደሆነ ለማወቅ የፖሊስ፣ የኬሚካል ባለሙያዎችና የዱር እንስሳት ባለሙያዎች የጋራ ምርመራ ቀጥሏል።

ይህ ክስተት በኬንያ የሰውና የዱር እንስሳት ግጭትን እንደገና ወደ ፊት አምጥቶታል። በአምቦሴሊ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ከዝሆኖች ጥቃት ለመጠበቅ አንዳንድ ጊዜ አደገኛ ኬሚካሎችን መጠቀማቸው ከዚህ በፊትም ተመዝግቦ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዚህ ክስተት የተከሰተው ሆን ተብሎ የተፈጸመ ድርጊት መሆኑ ገና አልተረጋገጠም።

በመጀመሪያ ምርመራ ላይ ከ15ቱ ዝሆኖች መካከል አምስቱ ሬሳዎች በጣም ስለበሰበሱ ወይም በአዳኝ እንስሳት ስለተበሉ ሙሉ የላቦራቶሪ ምርመራ ለማድረግ አልተቻለም። ይህም የምርመራው ውጤት አሁንም የመጨረሻ እንዳልሆነና ተጨማሪ ሳይንሳዊ ማረጋገጫዎች እንደሚጠበቁ ያሳያል።

የጥበቃ ባለሙያዎች ይህን ክስተት በአምቦሴሊ የሥነ ምህዳር አካባቢ በቅርብ ዓመታት ከተመዘገቡ እጅግ ከባድ የዱር እንስሳት መመረዝ አደጋዎች አንዱ መሆኑን በመግለጽ፣ በግብርና ውስጥ የሚጠቀሙ አደገኛ ኬሚካሎች አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ሔኖክ ወ/ገብርኤል#Ethiopia #GetuTemesgen #GetuNews#Kenya #elephants #Cyanide #KWS


Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: