#Ethiopia | አዲስ አበባ – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት በቦሌ ኆኀተ ብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ላለፉት አምስት ሳምንታት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መሠረታዊ የቤተክርስቲያን ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ ከ100 በላይ ታዳጊዎችን ሐምሌ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ የመገናኛ ብዙኃኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቀሲስ አካልወልድ ተሰማ እና የተመራቂዎቹ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
ተማሪዎቹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የቤተክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ታሪክ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የተማሩ ሲሆን፣ መርሐ ግብሩ እምነቱን ለወጣቶች ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ባለው መልኩ ለማስተላለፍ በማሰብ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት፣ ታዳጊዎች የእምነታቸውን ትምህርት በእንግሊዝኛ መማራቸው ወደፊት በውጭ ሀገራት ቢኖሩም እምነታቸውን በቀላሉ እንዲረዱና እንዲያስተምሩ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅትም የወንጌል ትምህርቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ የማድረግ ሥራውን በቀጣይነት እንደሚያጠናክር አስታውቋል።

Source: GetuTemesgen









No comments yet.