📌 የአባቶች በዓት ግንባታ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ለመግባት ምን ቀረው?
ክፍል ፫
#Ethiopia | በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት በምስራቅ በለሳ ወረዳ የሚገኘው ታሪካዊው የሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ብቻ ሳይሆን ራሱን በራሱ ለመቻልና ለቀጣዩ ትውልድ የሚመጥን ዘመናዊ መዋቅር ለመዘርጋት ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። ገዳሙ አጠቃላይ ሶስት ዋና ዋና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሁለተኛው ዙር የአባቶችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ የግንባታ ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ባለፈው በክፍል ሁለት የእናቶችን በዓት የደረሰበትን የግንባታ ሂደት የተወሰነውን ማስነበባችን የሚታወስ ነው በዛሬው ክፍል ሶስት በገዳሙ እየተገነባ የሚገኘውን የአባቶች በዓት (ማረፊያ) ያለበትን ወቅታዊ ቁመና፣ የተከናወኑ ስራዎችን እና ወደፊት የሚጠብቁትን ተግባራት እናያለን።
በገዳማዊ ህይወት ውስጥ ለአባቶችም ሆነ ለእናት መነኮሳት ምቹና የተረጋጋ የመኖሪያ ከባቢ መፍጠር መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በገዳሙ ሁለተኛ ዙር ግንባታ ውስጥ ትኩረት የተደረገበት ይሄው የአባቶች በዓት ግንባታ፣ አሁን ላይ አብዛኛው መዋቅራዊ አካሉ ተጠናቆ የማጠናቀቂያ ስራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አጠቃላይ ዲዛይኑም የገዳሙን ስነ-ስርዓትና ጥንታዊ የህንጻ ጥበብ ባገናዘበ መልኩ የተቃኘ ነው።
ብዙዎች ግንባታው ሲጀመር “ለምን ቅድሚያ ለእናት መነኮሳት ተሰጠ?” የሚል ጥያቄ ያነሱ ነበር፤ ሆኖም ለዚህ ምክንያቱ የቤተክርስቲያን አባቶች በተፈጥሮ እና በባህሪ ወንድ ልጅን እንደ አቅራቢ፣ ጠባቂና መጋቢ አድርገው ስለሚመለከቱትና እናቶች ደግሞ በተፈጥሯቸው ለተለያዩ ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጋላጭነቶች የቀረቡ በመሆናቸው ነው። እናቶች መነኮሳት ከምንኩስና ስራቸው በተጨማሪ የተፈጥሮ ኃላፊነቶች ስላለባቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በዓታቸው ተጠናቋል፤ አሁን ደግሞ ከዚያ በተቀሰመው መልካም ተሞክሮ የአባቶች በዓት ግንባታ እጅግ በተዋበና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
♦️ የተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች
እስካሁን ባለው ሂደት የአባቶች በዓት እያንዳንዱ ክፍል ባለ 12 ካሬ ሜትር ሆኖ አራት መነኮሳትን በነጻነት ለማስተናገድ በሚያስችል ስልታዊ አደረጃጀት ተገንብቷል። ከተለያዩ ገዳማት አድባራት ለልምድ ልውውጥና ለትውውቅ የሚመጡ እንግዶችን በክብር ለመቀበል ይረዳ ዘንድ፣ በማዕከል ላይ የሚገኘው አንደኛው ክፍል ብቻ ባለ 18 ካሬ ሜትር ሆኖ እንዲሰራ ተደርጓል። ይህ ክፍል ለተራ እንግዳ ሳይሆን ለገዳማውያን የእንግዳ መነኮሳት ማረፊያ ተብሎ የተለየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የህንጻዎቹ የጣራ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ለአባቶች ንጽህናና ጤና አጠባበቅ የሚያገለግሉ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችና የሻወር ክፍሎች ግንባታም ተጠናቆ መገልገያ እቃዎቻቸው በሙሉ ተገዝተው መጋዘን የገቡ ሲሆን፣ አሁን ላይ የመገጣጠም ስራዎች ብቻ ነው የቀሩት።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የተገነቡት ክፍሎች እስከ 64 የሚደርሱ አባቶችን ማስተናገድ የሚችሉ በመሆናቸው አሁን ላለው የመነኮሳት ቁጥር የአባቶች በዓት ሙሉ በሙሉ በቂ ሆኖ ተገኝቷል።
በዚህ ዙር ከተከናወኑት ስራዎች መካከል ሌላው የማምረቻ ሼድ ወይም የገዳሙ የቴክኒክና ምህንድስና ዲፓርትመንት ማዕከል ግንባታ ነው።
ከከተማ ርቆ በሚገኘው በዚህ በረሃ ውስጥ የሚሰበሩና የሚበላሹ በሮችንና የብረት መዋቅሮችን ለመጠገን ወደ ከተማ መመላለስ ከፍተኛ ወጪ ስለሚያስከትል፣ አባቶች ራሳቸው ስኳድራ መለካት፣ መቁረጥና መበየድ እንዲችሉ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ቀደም ሲል የሚመጡ ባለሙያዎች የአካባቢው የአየር ንብረትና ለምግብ ሁኔታ የማይመቹ ከመሆናቸውም በላይ ተጨማሪ ወጪ ይጠይቁ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ገዳሙ በገዛ አቅሙ የእንጨትና የብረት ውጤቶችን ማምረት የሚያስችልበትን ይህንን ሼድ አጠናቆ ማሽነሪዎቹን በሙሉ አስገብቷል።
በተጨማሪም አጋፔ ማዕድ ወይም መነኮሳቱ በጋራ ጸሎት አድርገው፣ ቡራኬ ይዘው ማዕድ የሚቀምሱበት ታላቅ አዳራሽ ግንባታ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታውን ጨምሮ በአብዛኛው አልቋል።
የሊቃውንት ማደሪያ ተብለው የተለዩት ዘጠኝ ክፍሎችም እንዲሁ ግንባታቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቤተክርስቲያን የስልጣን እርከንና ስርአት መሰረት ካህናቱና ዲያቆናቱ በተለየ መልኩ እንዲያርፉበትና ምልከታቸው በቀጥታ ወደ ቤተክርስቲያኑ እንዲሆን ተደርገው በከፍታ ቦታ ላይ ተገንብተዋል።
♦️ ያጋጠሙ ፈተናዎች
ግንባታው በተወሰነ መልኩ የጊዜ መጓተት ያሳየው በሀገሪቱ ባለው አጠቃላይ የሲሚንቶ ምርትና አቅርቦት እጥረት ምክንያት ሲሆን፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የገዳሙ አስተዳደር ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሲሚንቶ በስፋት ወደ ገዳሙ ማስገባት የሚጀመር ሲሆን፣ ግንባታው መሰረቱና መዋቅሩ አስቀድሞ ያለቀ ስለሆነ የልስን ስራው ብዙ ጊዜ የሚወስድ አይሆንም። የልስን ስራው በከፍተኛ ፍጥነት ተጠናቆ ባለሙያዎች አስቀድመው ወደተዘጋጁበት የቻክ (የጂብሰም) ስራ በቀጥታ ይሸጋገራሉ።
ይህ የጂብሰም ስራ እንደተጠናቀቀ የቀሩት የቀለም ስራዎችና የውስጥ ምንጣፎችን የማንጠፍ ስራዎች በፍጥነት የሚከናወኑ ይሆናል። ለክፍሎቹ የሚያስፈልጉ ምንጣፎች፣ መጽሐፍ ቅዱሶችና ዳዊቶች በሙሉ ቀደም ብለው ተገዝተው የገቡ በመሆናቸው፣ እነዚህ የማጠናቀቂያ ስራዎች ተጠናቀው ህንጻዎቹን ወደ አገልግሎት ማስገባት ብቻ ነው የሚጠበቀው።
ይህ ተግባር ከአካባቢው ጥበቃና ውበት ጋር አብሮ የሚሄድ በመሆኑ፣ ክፍሎቹ ሲጠናቀቁ ዙሪያቸውን በችግኞችና በአጸዶች የመሸፈንና የማስዋብ ስራ በእናት በአባቶች
መነኮሳትና የጋራ ተሳትፎ በስፋት ይከናወናል።
♦️ በቀጣይ በአባቶች በዓት የሚሰሩ ታላላቅ እቅዶች
ገዳሙ በአሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ በላይ መነኮሳትን የያዘ በመሆኑ፣ ወደፊት ለሚመጡት ተጨማሪ መነኮሳትና የአብነት ተማሪዎች የሚሆን የመኖሪያ ቤት መስራት የሚቻለው ገዳሙ የኢኮኖሚ ነጻነቱን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው። ስለሆነም ወደፊት የሚመጡ መነኮሳት በዚህ በማምረቻ ሼድና በተዘረጉት የልማት ማሽነሪዎች ተጠቅመው በራሳቸው አቅም ተጨማሪ በዓታትን እንዲገነቡ ይደረጋል። ይኸውም ዘመኑን የዋጀና ለቀጣዩን ትውልድ የሚሆን ጠንካራ የልማት መሰረት ለመጣል ታስቦ የተዘጋጀ ስትራቴጂ ነው።
ሁሉም ፕሮጀክቶች የሚከናወኑት በእኩል ደረጃ ሲሆን፣ አላማው ቤተክርስቲያኑን ብቻውን መጨረስ ሳይሆን የአባቶችን መረጋጋትና የገዳሙን የውስጥ ኢኮኖሚ አብሮ ማሳደግ ነው። አባቶች በዓት አጥተው በየበረሃው እንዳይበተኑና የካህናት ደሞዝ፣ የዕጣን፣ የጧፍና የዘቢብ ወጪዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ወደፊትም በስፋት ይቀጥላሉ። ገዳሙ እንደ ከተማ አድባራት ከምዕመናን ሙዳየ ምጽዋትና ሕዝባዊ የገንዘብ ማሰባሰብ ብቻ የሚተዳደር ባለመሆኑ፣ ራሱን እንዲችል ማድረግ የወደፊቱ ትልቁ ግብ ነው።
በተጨማሪም በአባቶች በዓት ዙሪያ የሚገኘውን ገደላማ ቦታ ለማቋረጥና መነኮሳቱ እንዲሁም ቀላል እንስሳት በቀላሉ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ፣ በብረት የሚሰራ ዘመናዊ ተንጠልጣይ ድልድይ የመገንባት ስራ ወደፊት የሚሰራ ይሆናል።
ቀደምት ክፍሎችን ለማንበብ ከስር ያለውን ሊንክ ይጫኑ
ክፍል ፩
https://www.facebook.com/share/p/1BaRxiEh2N/
ክፍል ፪
https://www.facebook.com/share/p/1MXrcbSRwK/
ገና በቀጣይ ቦታው ድረስ ሂደን የተመለከትነውን የህንጻ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ ከምን እንደደረሰ ፣ በገደሙ በቅርበት በሚገኘው ዙ ሐሙሲት ከተማ ትኩረቱን ትምህርት እና ጤና ላይ አድርጎ በግንባታ ላይ ስለሚገኘው ግዙፍ ኘሮጀክት የምንነግራችሁ ይሆናል።
አልተጠናቀቀም …..ይቀጥላል……
ጌትነት ተመስገን
📷 ከበደ መክብብ
Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን)
#የሙትአንሳማርቅዱስሚካኤልገዳም
#ማዕከላዊጎንደር #ምስራቅበለሳ #getu
#getutemesgen #ጌጡ #EastBelesa
#MuteAnsaMarStMichaelMonastery
#CentralGondar #EthiopianOrthodoxChurch





Source: GetuTemesgen







No comments yet.