#Ethiopia | ይህ እንደሃያሲ መፅሐፉ እንዴት እንደተፃፈ ለመፈተሽ የቀረበ ትንተና አይደለም፡፡ እኔ እንዴት እንዳነበብኩት ለመግለፅ እንጂ…
እንደ እኔ ንባብ ከሆነ የደራሲ ቤተ-ማሪያም ተሾመ “ቡናዬ እስኪሰክን” እንደኦሎምፒክ አርማ በብዙ ህብረ ቀለማዊ ክብ ቀለበቶች የተሞላ መፅሐፍ ነው፡፡
መፅሐፉ በአእምሮ ውስጥ እንደጅረት የሚፈስን ሃሳብ ተከትሎ የሚጓዝ ዓይነት ነው፡፡ በሰው አእምሮ ውስጥ እንደጅረት የሚፈሱት ሃሳቦችና ስሜቶች ከጅረቱ በተቃራኒ ከሚጓዙት ድርጊቶችና ንግግሮች ጋር ትይዩነት አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እነዚህን የተቃረኑ ቁርኝቶች ጮክ ብለን አናወራቸውም፡፡ በአእምሯችን ሸለቆ ውስጥ ተቀብረው ይፈሳሉ እንጂ…
በዚህ መፅሐፍ ግን በፍሰታቸው ውስጥ የራሳቸውን ክብ እየፈጠሩ ያልፋሉ እንጂ ቀጥ ብለው አይጓዙም፡፡ በአጭሩ ይህ መፅሐፍ የብዙ ክብ ታሪኮች ስብስብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ክቦቹ ከህይወታችንና ከታሪካችን የተቀዱ ናቸው፡፡
ክብ በሆነ መንገድ ላይ ስንጓዝ የትም አንደርስም፡፡ ከማያቋርጠው ድግግሞሽ የተነሳ ዞረን ዞረን እዛው ነን፡፡ ደራሲው በቡናዬ እስኪሰክን መፅሐፉ ቀጥ ብሎ ወደ ሆነ ግብ የሚያመራ ታሪክ አያሳየንም፡፡ ከዋናው ገፀ ባህሪይ ስሜት እና ፍላጎት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ታሪኮች የራሳቸውን ክብ እየሰሩ ይጠናቀቃሉ፡፡
ለምሳሌ ሚስቱ ጠዋት ያሳየችውን የተሸመደደ ጠባይ ማታም ትደግመዋለች፡፡ በማለዳው የቡና ስኒ የተጀመረው ታሪክ ዞሮ ዞሮ እዚያው ሲኒ ላይ ያከትማል፡፡ በታሪኩ መጀመሪያ አካባቢ የአደጋ ማስጠንቀቂያ የደረሰው ሰውዬ መጨረሻ ላይ አደጋውን ያስተናግዳል፡፡ በአስመራው ባሬስታ ላይ የደረሰው ነገርም በለሚ ኩራው ባሬስታ ላይ ይደገማል፡፡ የጀብሎዎቹና የሊስትሮዎቹ ምሬትና አመፅም በሀገሪቱ ግዙፍ የታሪክ አዙሪት ተውጦ ይቀራል፡፡ የአታክልቲ መጨረሻም እንዲሁ፡፡
መፅሐፉ በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥም ዞሮ ዞሮ ያው የሆነውን የመበላላት አዙሪት ያነሳል፡፡ በኮሎኔል መንግስቱና በእነተፈሪ ባንቴ መካከል የተፈጠረውን… በህወአት አመራሮች የእርስ በእርስ ግጭት የተደገመውንና በቅንጅት መሪዎች የተሰለሰውን የመበላላት አዙሪት ይታዘባል፡፡
የዋናው ባለታሪክ አለም አቀፍ ግንዛቤዎች ጭምር ዞሮ ዞሮ እዛው በሆነ የታሪክ አዙሪት የተዋጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ማ ቤከርን ያነሳል፡፡ ቦኒየሞች የዘፈኑላት ማ ቤከር በዘመኗና በመንደሯ የበረታው ግፍና ወንጀል አስመርሯት ከአራት ልጆቿ ጋር አመፅ ማስነሳቷን ይነግረናል፡፡ ድል አድራጊው የማ ቤከርና የልጆቿ ስኬታማ አመፅ የሚጠናቀቀው ግን ያንኑ ግፍና ወንጀል በመድገም ነው፡፡
የስኒውን ምልኪ ጨምሮ በቡናዬ እስኪሰክን ደጋግመን የምናገኛቸው እንደ ውርርድ፣ እጣ ፋንታና የአርባ ቀን እድል ዓይነት ቃላት ራሳቸው የክብነት ባህሪይ አላቸው፡፡ ንግርት ሁሌም የሚነግርህ የፈለግከውን ያክል ብትፍጨረጨር ከተፃፈልህ እጣ ፋንታ እንደማታመልጥ ነው፡፡
የሰው ልጅ የሚሆነውን ነገር ለምን እንደሚሆን የሚረዳበት አእምሮ እና ተጨባጭ ምክንያት ሲያጣ የምልኪ ፣ የጥንቆላና የአርባ ቀን እድል ሰለባ ይሆናል፡፡ በማይቆጣጠረው የህይወት አዙሪት ውስጥም ይወድቃል፡፡
በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተፈጠረው የሃሳብና የታሪክ አዙሪት መፅሐፉን አሰልቺ አለማድረጉ ይልቁንም ጣእሙን እንዳሳመረ እስከመጨረሻው የመዝለቁ ነገር የፅሁፌ ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ይህን የማነሳው አለምክንያት አይደለም፡፡
ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ፈር ቀዳጅ የተባሉ አንዳንድ የስነ-ፅሑፍ ሙከራዎች አንባቢን የማታከት ባህሪይ ይታይባቸዋል፡፡ አንዱን ሲይዙት ብዙ ያመልጣቸዋል፡፡ በእኔ እምነት የተሟላ ፈር ቀዳጅ ስራ ነጠላ መልክም ትርጉምም የለውም፡፡ ቢያንስ አምሰት ተጨማሪ ሙላቶች አሉት፡፡ ስድስተኛውም እጅግ ይመረጣል እላለሁ፡፡
-የመጀመሪያው የቋንቋ ውበት ነው፡፡ ቋንቋው ካላማረህ ጀምረህ አትጨርሰውም፡፡ በዚህ መፅሐፍ ዋናው ባለታሪክ ህይወትን አሟጦ ሲኖር አይታይም፡፡ ኑሮን በቀጥታ የመጋፈጥ ድፍረት ይጎለዋል፡፡ በአብዛኛው የታሪኩ ክፍል ሲሸሽ እንጂ ሲያሳድድ አናየውም፡፡ ሌላው ቀርቶ የተላኩለትን ሁለት አጓጊ ደብዳቤዎች እንኳ አንብቦ የመጨረስ ድፍረት የለውም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዋና ገፀ-ባህሪይ ይዞ ማራኪ ታሪክ መፍጠር ይከብዳል፡፡ ያም ሆኖ የደራሲው ቋንቋ ቀላል እና ውብ ስለሆነ ሳይሰለቸን እንዲያውም ደስ እያለን እናነበዋለን፡፡
-ሁለተኛው የሃሳብ ጉልበት ነው፡፡ በሃሳብ ጥልቀት የዳበሩ መፅሐፎችን ስናሰላስላቸው እንከርማለን እንጂ አንብበን አንጨርሳቸውም፡፡ “እግሮችህ የአንተ ናቸው፡፡ ወዳሻው የሚራመድበት ግን ሌላ ነው” የምትለው የመፅሐፉ ደማቅ አረፍተ ነገር ተነባ የምታልቀው መቼ ነው?
-ሶስተኛው የትውልድና የዘመን ነፀብራቅነት ነው፡፡ አፈወርቅ ገብረ እየሱስ የባሪያ አሳዳሪውን ዘመን… ሃዲስ አለማየሁና ዳኛቸው ወርቁ የፊውዳሉን… በአሉና ብርሃኑ ዘሪሁን የአብዮቱን ዘመን ከነሙሉ ጠረኑና ለዛው እንደፃፉልን ሁሉ ቤተ-ማሪያምም የኮሪደር ዘመኗን አዲስ አበባ ፊልም በሚመስል ትእይንት ያሳየናል፡፡
-አራተኛው ከውስጥ የመነጨ ልዩነት ነው፡፡ ለየት ለማለት ብሎ ከእውነታውም ከችሎታውም ከማንነቱም ከስሜቱም የራቀ ደራሲ ህያው እስትንፋስ ያለው የጥበብ ስራ ሊያቀርብልን መቻሉን እጠራጠራለሁ፡፡ እንዲያውም በእኔ እምነት መለየት የሚባለው ነገር ፈልገህ የምታገኘው ሳይሆን ተለይተህ የምትገኝበት ወይም የምትፈጠርበት ዓለም ነው፡፡ ቤተ-ማሪያም ተሾመ በጠያይም መላእክትም ሆነ በዚህኛው መፅሐፉ ተለይቶ የተፈጠረ ወዛም ደራሲ እንጂ ለመለየት የተፍጨረጨረ ችኮ ብእረኛ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
-አምስተኛው ውስጡ የሰፋ ስስነት ነው፡፡ ራስህ ካልተቆነጠጥክ በቀር ህመም የማይሰማህ ከሆነ አንተ ዳያሪ ፀሃፊ እንጂ የተዋጣለት ደራሲ የመሆን እድልህ ጠባብ ነው፡፡ ለትልቅነት የታጨ ደራሲ በቤቱ ብቻ ሳይሆን በጎረቤቱ… በሰፈሩ ብቻ ሳይሆን በሀገሩ የመጣ ቁንጥጫ ያመዋል፡፡ ከዚያም አልፎ የሰው ልጅ ውጋት ይቀስፈዋል፡፡ ከእኛ ዘመን እና ሀገር የራቁ ታላላቅ ደራሲያን በሌላ ቋንቋ ፅፈው ስሜታቸውን የሚያጋቡብን ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ቤተ-ማሪያም ተሾመ በሰፈሩም በሃገሩም የሚሆነው ነገር የሚሆነውን የሚያሳጣው ዓይነተ ደራሲ መሆኑን ከስራዎቹ መረዳት ችያለሁ፡፡
በዚህ ዓይነት ደረጃ ከመሰጡኝ የሀገራችን ደራሲያን ግን የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ታሪክ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ያገኘሁት ከፍቅር እስከ መቃብር በኋላ ያነበብኩትን የዳኛቸው ወርቁን አደፍርስን ነው፡፡ በአጭር ልብ-ወለድ ዘርፍም ከስብሃት ገብረእግዚአብሔር በኋላ ያነበብኳቸው የአዳም ረታ አጫጭር ልብ -ወለዶች በእኔ እይታ የኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ፈር ቀዳጅ ስራዎች ናቸው፡፡ በተለይ አለንጋና ምስር ውስጥ ያሉት…
ከእነዚህ ሁለት ታላላቅ ደራሲያን ስራዎች በኋላ በተሟላ ሁናቴ ፈር ቀዳድ ሆኖ ያገኘሁት የቤተ-ማሪያም ተሾመን ቡናዬ እስኪሰክን ነው፡፡
ቤተ-ማሪያም በዚህ መፅሐፉ ከተጠቀማቸው ቃላት በላይ ብዙ ፅፏል፡፡ በበኩሌ አንድን ስራ ምርጥ ስነ-ፅሁፍ ከምልባቸው ምክንያቶች ስድስተኛው በትንሽዬ መፅሐፍ ውስጥ ብዙ ሺህ ገፆች ሲያስነብበኝ ነው፡፡
ለጆርጅ ኦርዊል አኒማል ፋርም… ለሚካኤል ቡልጋከቭ ሳባቺዬ ሴርሴ… ለሄሚንጉዌይ ሽማግሌውና ባህሩ… ለቼሆቭ ዋርድ ነበር ሲክስ… ለቶልስቶይ የኢቫን ኤሊይች እረፍት… ለአልበርት ካሙ ባይተዋር… ከፍተኛ አድናቆት ያለኝ ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
ቡናዬ እስኪሰክን ከላይ ከገለፅኳቸው መፅሐፎች ጋር የሚመጣጠን ልዩ እርካታ ፈጥሮብኛል፡፡ በእያንዳንዱ አዙሪት እያሽከረከረ እኛንም ዘመናችንንም ሀገራችንንም በጥልቀትና በድምቀት ያሳየ ስራ በመሆኑ…
በነገራችን መሀል በቤተ-ማሪያም ተሾመ ቡናዬ እስኪሰክን የክብ ታሪኮች ጅረት የመጨረሻ ገፅ ላይ ያሉት የመጨረሻዎቹ ሁለት መጠይቃዊ ቃላት ራሳቸው አዙሪቱ የፈጠረውን ተደጋጋሚ ክብ አሳስበውኛል፡፡
“… ተጀመረ? ወይስ ተፈፀመ? …” ይላሉ፡፡
ህይወትም ታሪክም ፖለቲካም ክብ ሲሆንብህ እንዲህ ትጠይቃለህ፡፡
ክቡ የት ጋ እንደሚጀምር አታውቅም፡፡ የት ጋ እንደሚጠናቀቅ ጭምር፡፡
Source: GetuTemesgen








No comments yet.