አዲስ አበባ የፌዴራል መንግስት ተጠሪ እንድትሆን ከስምምነት ሲደረስ፣ “የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ትሁን” ለሚለው ሁለት አማራጮች ቀርበው የአዘጋጅ ቡድኑ ቃለጉባዔ ተነበበ።
35ኛ ቀኑን ባስቆጠረው ዋናው የምክክር ጉባዔ በ10፣ 50፣ 250፣ 500 ሰዎች በያዙ ቡድኖች ተመካካሪዎች ሲመክሩባቸው የነበሩ ምክረ ሀሳቦች 500 ሰዎች ከያዘው ቡድን ከደረሱ በኋላ ቡድኑ ተመካክሮባቸው ከስምንቱም ቡድኖች ለተመረጡ 120 አባላት ላሉት ምክረ ሀሳቦች አዘጋጅ ቡድን መቅረባቸው ይታወሳል።
120 አባላት ያሉት ምክረ ሀሳብ አዘጋጅ ቡድን ከባለ 500ው ቡድን የተቀበላቸውን የተመካካሪዎች ምክረ ሀሳቦች ካጣጣመ፣ የሚያቃረኑ ነገሮች እንዳይኖሩ ከተጠነቀቀ፣ ወደ አንድ ወጥ ምክረ ሀሳብ እንዲመጡ ካደረገ በኋላ 500 ሰዎች ለያዙ ለእያንዳንዱ 8 ቡድኖች አቅርቦ ከተመካካሪዎች ሰሞኑን ግብዓት ሰብስቧል።
በዛሬው መርሃ ግብር ደግሞ፣ 120 አባላት ያሉት ቡድን ያዘጋጀውና ግብዓት የሰበሰበበት ቃለጉባዔ ለእያንዳንዱ 500 ሰዎች ለያዙ 8 ቡድኖች ተነቧል። እያንዳንዱ 8 ቡድኖች ሲመክሩ የቆዩት በአንድ፣ አንድ አጀንዳ ሲሆን፣ ዛሬ በተነበባቸው ቃለጉባዔ የተመካከሩበትን አጀንዳ ጨምሮ ያልተመካከሩባቸው የ7ቱ አጀንዳ ምክረ ሀሳቦችም በአዘጋጅ ቡድኑ ተዘጋጅተው ቀርበውላቸዋል።
አከራካሪ ሆኖ በቆየው የአዲስ አበባ ጉዳይ ዛሬ በተነበበው ቃለጉባዔ ምን ተባለ ?
ስምንቱ ዝርዝር ሀሳቦች ከያዙ ዋና አጀንዳዎች መካከል በፌዴራል ከተሞች ጉዳይ፥ የአዲስ አበባ እና የድሬዴዋ ጉዳይ አንዱ ነው። በዚህም በተለይ የአዲስ አበባ ህጋዊ ጉዳይ በተመካካሪዎች በኩል ብርቱ ክርክር፣ ጭቅጭቅ፣ ምክክር ሲያስተናግድ ሰንብቷል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ዛሬ ከምክክሩ ተሳታፊዎች እንደተረዳው፣ አዲስ አበባ ተጠሪነቷ የፌዴራል ከተማ ይሁን የሚለው ጉዳይ ተመካካሪዎችን ያስማማ በሚል በቃለባዔው ተቀምጧል።
ልዩ ጥቅም የሚለው ደግሞ “የጋራ ጥቅም” በሚለው ተተክቶ አስማምቶ ቀርቧል። ከተማዋ የፌዴራል ከተማ መሆኗ እንዳ ሆኖ፣ ሌሎች ከተሞች ይጨመሩ የሚል ምክረ ሀሳብም ተቀምጧል።
የኦሮሚያ ክልልን የወከሉ ተሳታፊዎች “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትሆን ሕገመግስቱ እውቅና ይስጥ” ሲሉ፣ ሌሎች ተመካካሪዎች ደግሞ፣ “አዲስ አበባ የብሔር ብሔረሰቦች ናት። ለአንድ ክልል ብቻ አትሰጥም” በሚል ተከራክረው ሀሳቡ በልዩነት ተይዞ እንደነበር ይታወቃል።
ዛሬ በተነበበው የስምንቱንም አጀንዳ ምክረ ሀሳቦች አጣጥሞ የቀረበው ቃለጉባዔ፥ “አዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ዋና መቀመጫ” እንድትሆን በቀረበው ምክረ ሀሳብ ሁለት አማራጭ ምክረ ሀሳቦች እንደተቀመጡለት ተገልጿል።
አንደኛው፥ “ሁሉም ክልሎች ርዕሰ ከተማቸውን መምረጥ ይችላሉ” የሚለው በሕግ ይደንገግ የሚል ነው።
ሁለተኛው፥ በአንቀጽ 49/5 አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በከተማዋና በክልሉ መካከል ያለው ግንኙነት በሕግ ይደንገግ የሚል መሆኑ ተመልክቷል።
የድሬዳዋ ከተማን ጉዳይ በተመለከተ ደግሞ፣ ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግስቱ እንዲሆን፣ ሕገመንግስቱ እውቅና በሰጠው ቻርተው እንድትተዳደር በቃለጉባዔው ተነቧል።
ዛሬ የተነበበው የተነበበው ቃለ ጉባዔ ነገ በ4ሺሕ ጉባያኞች ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
@tikvahethiopia
Source: Yeneta Tube









No comments yet.