የሲዳማ ዘመን መለወጫ እና የሲዳሙ አፎ አጀንዳዎች በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ውድቅ መሆናቸው ተነገረ

- Advertisement -
Sidebar AD

#Ethiopia | የፍቼ ጫምባላላ በዓል በብሔራዊ ካላንደር ውስጥ እንዲካተት እና የሲዳሙ አፎ የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን የቀረቡት አጀንዳዎች በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጉባኤ ውይይት ሳይደረግባቸው ውድቅ መደረጋቸው ታወቀ።

በምክክሩ መጀመሪያ ላይ በአንዳንድ ተሳታፊዎች ጥረት ሁለቱ ነጥቦች በአጀንዳነት ተይዘው የነበረ ቢሆንም፣ ከክልሉ የመጡ አብዛኞቹ ባለሥልጣናትና የፓርቲ ተወካዮች አስፈላጊውን የመከራከሪያ ሀሳብ ባለማቅረባቸው ምክንያት አጀንዳዎቹ ወደ አራት ሺህ አካባቢ ወደሚሆኑት ዋና ተመካካሪዎች ሳይደርሱ ቀርተዋል።

በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የፍቼ ጫምባላላ በዓል በብሔራዊ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ በካላንደር እንዲካተት የቀረበውን ሀሳብ በተመለከተ፣ የክልሉ ተወካዮች ድርጅታችን በዚህ ጉዳይ ላይ ተልዕኮ አልሰጠንም በሚል ዝምታን መምረጣቸው አጀንዳው ውድቅ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።

በተጨማሪም በስብሰባው ላይ የተገኙት የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ተወካዮች እንድንከራከር አልተነገረንም በሚል ምክንያታዊነት ሀሳቡን ሳይደግፉ መቅረታቸውን ተሳታፊዎች በቁጭት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በዩኔስኮ ያልተመዘገበው የኢሬቻ በዓል በሀገሪቱ ካላንደር ውስጥ እንዲካተት የቀረበው አጀንዳ አልፎ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው የፍቼ ጫምባላላ በዓል ውድቅ መደረጉ የክልሉ ተወካዮች ያሳዩትን ከፍተኛ ቸልተኝነት እንደሚያሳይ ተጠቅሷል።

የሲዳሙ አፎ የሀገር የሥራ ቋንቋ እንዲሆን የቀረበው ሀሳብም ቢሆን በቂ የመከራከሪያ ድጋፍ አላገኘም። ከክልሉ ከተወከሉት ተመካካሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ለሲዳሙ አፎ ከማጎልበት ይልቅ የወላይታ ቋንቋ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ጠንካራ መከራከሪያ ሲያቀርቡ እንደነበር የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል።

ለሲዳሙ አፎ ያልተከራከሩበትን ምክንያት ሲጠየቁም አንዲቷ ተወካይ ጠባብ ተብዬ እንዳልፈረጅ በማለት የሰጡት ምላሽ ተሳታፊዎችን ማበሳጨቱ ተገልጿል።

በአጠቃላይ ከክልሉ የተወከሉት ባለሥልጣናትና ተሳታፊዎች ያሳዩት አቋም፣ የቋንቋ እና የባህል አጀንዳዎቹ ወደ ዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እንዳያልፉ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል።

ሆኖም ግን የተወሰኑ የሲዳማ ተወካዮች ሁለቱ ነጥቦች በድጋሚ በአጀንዳነት ተይዘው እንዲቀርቡ የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙና አቤቱታቸውን ለኮሚሽኑ ለማስገባት በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

#sidama #ficheechambalaala #sidamuaffo #nationaldialogue #consultationcommission #ethiopianews
#getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa






Source: GetuTemesgen

Comments

No comments yet.

- Advertisement -
Advertisement post bottom2

You might want to listen to: