*ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፣
መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ።
#Ethiopia | ባልቻ ሳፎ በ1854 ዓ.ም ወሊሶ አገምጃ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ተወለዱ።
ከ14 ዓመታቸው ጀምሮ በሚኒሊክ ቤተ መንግስት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ሲሰሩ የቆዩት ደጅ አዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ድንቅ የኢትዮጵያ ልጅ የሚያስብላቸውን ገድል በወርቃማው ቀለም በኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ ላይ ጽፈዋል።
የአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት የሆነውን የአድዋ ድልና የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ታሪክ ህያው አድርጎ የሚዘክረው “ባልቻ አባ ነፍሶ” የተሰኘው ታሪካዊ ቴአትር በጀግናው የትውልድ ስፍራ በወሊሶ ከተማ አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ ለዕይታ ቀርቧል።
ይህ ልዩ ስሜት የሚፈጥርው የጥበብ ስራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉትን ባልቻ አባ ነፍሶን ወደር የለሽ ተጋድሎ የሚያንጸባርቅ ነው።
የቲያትሩ ዋና ትኩረት ጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ስር ለማድረግ ያደረገችውን ተደጋጋሚ ሙከራና በ1888ቱ የአድዋ ጦርነት የደረሰባትን አሳፋሪ ሽንፈት እንዲሁም ጀግናው ባልቻ አባ ነፍሶ በዳግም ወረራ ወቅት በነበራቸው አስደናቂ ተጋድሎ ለሀገራቸው ሲሉ የከፈሉትን የህይወት መስዋዕትነት በትውልዱ አዕምሮ ውስጥ መቅረጽ ነው።
ባልቻ አባ ነፍሶን ግራዚያኒ “ያገርዎ ንጉሥ የወረሰብዎትን ሀብት እንመልስልዎታለን፤ ወደ እኛ ይግቡ።” ብሎ ቢፅፍላቸው ባልቻ ግን፤
“… ይድረስ ለግራዚያኒ፤ ገንዘቤን አንተ ከምትመልስልኝ ያገሬ ንጉሠ ነገሥት የወረሰኝ እሱ ይሻለኛል። አንተንም በሞት እንጂ በህይወት አላይህም።” ብለውት ነበር።
ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉበትና በአዲስ አበባ ቲያትር ቤቶች አስተዳደር ከወሊሶ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ያቀረበው ይህ ታሪካዊ ቲያትር የተመልካቹን ስሜት ሰቅዞ የሚይዝ ነበር።
ታሪክን ከመተረክ ባለፈም የዛሬው ትውልድ አባቶቹ የከፈሉትን ከባድ መስዋዕትነት ተረድቶ ከዘረኝነት፣ ከድህነትና ከመለያየት አስተሳሰቦች በመውጣት የሀገሩን አንድነት እንዲያስጠብቅ ከመድረኩ ጥሪ ቀርቧል።
ትውልዱ የትላንት ታሪኩን በማወቅ የዛሬ ፈተናዎቹን በብቃት መወጣት ይችል ዘንድ ይህ ታሪካዊው የባልቻ አባ ነፍሶ ቲያትር ወቅታዊና ጥልቅ ሀገራዊ መልዕክቱን በተሳካ ሁኔታ አስተላልፏል።
በቲያትሩ የመክፈቻ መርሃግብር ላይ የወሊሶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገመቹ አረዳ ፣ የባልቻ አባ ነፍሶ የእህት ልጅ ልጅ ወ/ሮ ዝምታወርቅ ነጋሽ ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
”የባልቻ አባ ነፍሶ” ቲያትር በብርሃኑ ዘርይሁን ተጽፎ የዝግጅት ስራው በዶ/ር ተሻለ አሰፋ ተከናውኗል።
ለ Getu Temesgen – (ጌጡ ተመስገን) ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽንስ
ያፌት ገ/ህይወት
ከኦሮሚያ ፤ ወሊሶ ከተማ



Source: GetuTemesgen









No comments yet.